እኛ እና ሜሪካ !
የኢትዮጵያ እና የአሜሪካ ግንኙነት አንድ መቶ ዓመታትን የሚሻገር መሰረቱንም በአጼ ምኒልክ የንግሥና ዘመን ያደረገ ነው፡፡ በተለየ ሁኔታ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የንግሥና ዘመን የኢትዮጵያና የአሜሪካ ግንኙነት ከፍ ብሎ እንደነበር ታሪክ ምስክር ነው፡፡ በወታደራዊ በተለይም በባህር ኃይል፣ በመረጃ ቅኝትና በሜካናይዝድ ጦር አደረጃጀት አሜሪካ የኢትዮጵያ አጋር ሆና ቆይታለች፡፡ በንጉሡ ዘመን ለተማሪዎች ነጻ የትምህርት ዕድል በመስጠት አሜሪካን የሚበልጥ የኢትዮጵያ ወዳጅ ምዕራባዊ ሀገር የነበረ አይመስለኝም፡፡ ለዚህ ሁሉ ውለታ አሜሪካ ፍላጎቷ የቀይ ባህር ፖለቲካን ለመቆጣጠር ያኔ በኢትዮጵያ ግዛት ስር በነበረችው ኤርትራ ላይ ነጻ መሬት ማግኘት ነበር፡፡ በተጨማሪም ከጸረ-ቅኝ ግዛት ትግል ጋር ተያይዞ ወደአፍሪካ በፍጥነት እየተዛመተ የነበረው የግራ ዘመም ፖለቲካ አስተምህሮ በኢትዮጵያ እግሩን እንዳይተክል ለመከላከል በማለም ከንጉሡ ጋር የነበራትን ወዳጅነት አጥብቃ ነበር፡፡ ነገር ግን የለውጥ አስገዳጅነትን ተከትሎ መሰረቱን የተማሪዎች እንቅስቃሴ ያደረገው ለውጥ ሲመጣ፣ ኢትዮጵያ ባስተናገደችው አብዮት ደርግ ‹ክስተት› ሆኖ ቤተመንግሥቱን ተቆጣጠረ፡፡ እናም ደርግ ይከተል በነበረው የግራ ፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም የተነሳ ከካፒታሊስቷ አሜሪካ በተቃራኒ የነ ሶቭየት ሕብረት ወዳጅ በመሆኑ ኢትዮጵያና አሜሪካ ወዳጅነታቸው ሻክሮ ቆይቷል፡፡
በሌላ የታሪክ ፍሰት ታላቋን ትግራይ አልሞ በረሃ የገባው ትህነግ ከአሜሪካ አይን ለመግባት ጊዜ ቢወስድበትም የደርግ አፍቃሪ ሶቭየት ህብረትነት፤ አሜሪካውያን የማታ ማታ ትንሿን አልባንያን በምስራቅ አፍሪቃ ለመትከል ሞዴል አድርጎ የሽምቅ ውጊያ ውስጥ የገባውን ትህነግ ለማቅረብ ተገደዱ፡፡ ትህነግ የዓለም የፖለቲካ ለውጥ ሚዛን እና የደርግ የውድቀት ጉዞ አቅጣጫውን አቅንቶለት እንደ ጎርፍ ተነድቶ ምኒልክ ቤተ-መንግሥት ሲገባ የአሜሪካኖቹ ሚና በቀላሉ የሚታይ አልነበረም፡፡
ድኀረ-1983 የተተከለው የፖለቲካ ሥርዓት አሜሪካን ለመሰሉ የምዕራቡ ሀገራት የሚጎረብጥ አልነበረም፡፡ በስማዊ ዴሞክራሲ (pseudo democracy) እና በነጻ ገበያ ስም ወዳጅነቱን ማስቀጠል የቻለው የትህነግ አገዛዝ ከኢትዮጵያ አልፎ የቀጣናው አስፈላጊ ኃይል ሆኖ ለመታየት ብዙ ጥሯል፡፡ በተለይም በአልቃይዳ ከተፈጸመው የመስከረም አስራ አንዱ (9/11) የአሜሪካ መንትያ ህንጻዎች ጥቃት በኋላ you are either with us or with the terrorists በሚለው የአሜሪካኖቹ ኃይል አሰላለፍ ትህነግ የምዕራቡ ዓለም በተለይም የአሜሪካ አጋር ሆኖ በመቅረብ በአገር ውስጥ ይፈጽማቸው የነበሩ ግፎችንና አፈናዎችን መደበቂያው አድርጎ ቆይቷል፡፡ ምንም እንኳ በግዳጅ አፈጻጸሙ ላይ የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን ከፊት የተሰለፈበት ቢሆንም፣ በአፍሪቃ ሀገራት በነበሩ ሰላም የማስከበር ዘመቻዎችና አልሸባብን ከሶማሊያ በማጽዳቱ ሂደት ትህነግ ለምዕራባውያኑ ልዩ የቀጣናው ፖለቲካዊ ኃይል ሆኖ ታይቶበታል፡፡ አሜሪካውያኑም ሆኑ የምዕራቡ ዓለም አገራት ትህነግን በተጋነነ ሁኔታ ይመለከቱት እንደነበር ለማወቅ በአስራ አምስት ቀን ኦፕሬሽን መደምሰሱን ለማመን ሲቸገሩ ማየታችን ነው፡፡ ትህነግ በዚህ ፍጥነት ይሸነፋል ብለው አልገመቱም ነበር፡፡ የአውሮፓ ህብረትም ሆነ አሜሪካ የትህነግን ፖለቲካዊ ሽንፈት የተቀበሉ ቢሆንም ወታደራዊ ሽንፈቱ እንዲህ ቅርብ ይሆናል የሚል ግምት የነበራቸው አይመስልም፡፡
የትህነግ ውሎ ያደረ የዲፕሎማሲ ስምሪትና የተጋነነ ምስሉ በፈጠሩት ብዥታ ዛሬም ድረስ ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ስለኢትዮጵያ በተለይም ስለትግራይ ሁኔታ የተዛባ መረጃ ይዞ ይታያል፡፡ ለዚህም ነው የፌዴራሉ መንግሥት በትግራይ ክልል ያካሄደውን የህግ ማስከበር እንቅስቃሴ ተከትሎ በርካታ የተዛቡ መረጃዎች በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሲቀርቡ የምንመለከተው፡፡ በዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ የሚሰጡ መግለጫዎች ደግሞ ነገሮችን ግራ አጋቢ አድርገዋቸዋል፡፡ የተጠቃ የኢትዮጵያ ዋልታና መከታ የሆነው የአገራችን መከላከያ ሰራዊት፤ ፍጅት የተፈጸመው አማራዊ ማንትን መሰረት አድርጎ ሆኖ እያለ (ማይካድራና ሁመራ ላይ በአማራ ተወላጆች የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሟል) በአጠቃላይ ጥቃት የደረሰው በኢትዮጵያ እና በአማራ ላይ ሁኖ እያለ፤ አንዳንድ ወገኖችና የዓለምአቀፉ ማህረሰብ፤ በተለይም የአውሮፓ ሕብረት አሁን ደግሞ የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት እውነታውን ትተው ከሀሰት ጎን መቆማቸው ብዙዎችን ግራ አጋብቷል፡፡
እውነት ነው ትግራይ ውስጥ የተካሄደው ጦርነት እንጅ ኳስ ጨዋታ ባለመሆኑ በሂደቱ ጉዳት የደረሰባቸው ንጹሀን መኖራቸው አይቀርም፡፡ ያውም'ኮ ጦርነቱ የተካሄደው በጓንዴ፤ አልቢንና ምንሽር ሳይሆን፤ ሁለቱም ወገኖች (ትህነግና የኢትዩጵያ መከላከያ ሰራዊት) አገራችን በታጠቃቻው ዘመናዊ መሳሪያዎች ነው፡፡ ታድያ እነዚህ መሳሪያዎች ትግራይ ላይ ወድቀው ሰው ተጎዳ፤ ንብረት ወደመ የሚሉት ነገር እንዴት ነው? ይህ ሊሆን እንደሚችል የታወቀው እኮ ትህነግ የሰሜን ዕዝን ከጀርባ ካጠቃበት ስዓት ጀምሮ ነው፡፡ ያም ሁኖ ግን መንግስት በተቻለው አቅም ሁሉ መጠነ ሰፊ ውድመት እንዳይደርስ ኦፕሬሽኑን በጥንቃቄ በመምራቱ ሊደርስ የነበረውን የከፋ እልቂት መቀነስ ችሏል፡፡ አሁን ከተከዜ ወዲያ ማዶ ያለው መደበኛው የትግራይ ክልል ለዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች ለጉብኝት ነጻ ሆኗል፤ ወደ ትግራይ ያመሩት ጋዜጠኞችም ሲጮኸ በከረመው ልክ የእልቂት ዜና ማግኘት አልቻሉም፡፡
ትህነግ ማይካድራ ላይ ከአንድ ሺህ በላይ የአማራ ተወላጆችን እንደጨፈጨፈው የፌዴራሉ መንግሥት በትግራይ ሕግን የማስከበር ዘመቻ ወቅት ዘርን ላይቶ ጥቃት አልፈጸመም፤ የኦፕሬሽኑ ዋና ዒላማ የትህነግ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ኃይል ብቻና ብቻ ነበሩ፡፡ ነገር ግን በዚህ ሂደት ውስጥ የተጎዳ ወገን ሊኖር ይችላል፤ ግን ግን በዘሩ ምክንያት ነው ማለት አይቻልም፡፡ ጉዳት ይኖራል፤ የጉዳቱ መንስኤ ግን ሕዝብን ሰብዓዊ ምሽግ አድርጎ የተዋጋው ትህነግ ነው፡፡
እውነታው እየታወቀ፤ በዳይን እንደተበዳይ፤ ተበዳይን ደግሞ እንደ በዳይ የመመልከት ሁኔታ እየተስፋፋና እውነት እየመሰለ መጥቷል፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ተደርገው ሊታዩ የሚችሉት ከሰሞኑ እየወጡ ያሉ መገለጫዎች ናቸው፡፡ የሰሞኑ የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት መግለጫና እሱን ተከትሎ የወጣው የዛሬው የአረና መግለጫ ነባራዊ እውነታውን የካዱ መግለጫዎች ናቸው፡፡ እነዚህና ሌሎች መሰል መግለጫዎች ተበዳይን በዳይ፤ በዳይን ደግሞ ተበዳይ አድረገው የቀረቡ ኢ-ፍትሐዊ መግለጫዎች ናቸው፡፡ ይህ ሚዛናዊ ያልሆነ አካሄዳቸው በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ለጊዜው የተሳካላቸው አስመስሏቸዋል፡፡
ግን ለምን?
እነዚህ ወገኖች፤ እውነትን ደፍቀው ሀሰትን ያነገሱበት ምክንያት ምንድ ነው? ብሎ መርምሮ እውነታውን መፈተሸ አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ ይህ ደግሞ ለነገ የሚተው ስራ ሳይሆን ዛሬውኑ መጀመር ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ በኩል ኢትዮጵያን የሚወድ ዜጋ ሁሉ ኃላፊነት እንዳለበት ይሰማኛል፡፡ ሰዎች ውሸትን ፈጥረው እውነት በማስመሰል ማቅረብ ከቻሉ፤ እኛ በእጃችን ላይ ያለውን እውነታ ለሁሉም ወገኖች በማስረዳት፤ እንዴት እውነትን በእውትነቷ መጠበቅ ይሳነናል? ሁሉም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ፤ በተለይም ውሸት በነገሰበት የምዕራቡ ዓለም የሚኖረው ዲያስፖራ፤ ለአገሩ ክብር ሲል እውነታውን ለሚዲያዎችና ለዓለምአቀፍ ተቋማት ማሳውቅና የተጀመረውን የውሸት ዘመቻ ማክሸፍ ይኖርበታል፡፡ እንዴው በሞቴ በአሜሪካና አውሮፓ ሀገራት የሚኖር ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ከጥቂት ጽንፈኞች በቁጥር በ 1000% አይበልጥም? ይህ አገር ወዳድ ኃይል፤ እንዴት የሀሰት ዘማቾቹን ውሸት ማጋለጥ አቃተው?
ለሁሉም በክቡር አቶ ደመቀ መኮንን የሚመራው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በትላቱ እለት ለአሜሪካ መግለጫ የሰጠው ምላሽ ተመችቶኛል፤ እንደዛ ነው መባል ያለበት፡፡ ይሄም ሁኖ በዲፕሎማሲ ስራችን ለምን ይሄንን ያክል ያውም በዋሽቶ አደሮች እንዴት ብለጫ ተወሰደብን ብሎ መመርመር ተገቢ ይመስለኛል፡፡ በዚህ በኩል የግድ የፖለቲካ አመራር ሁኖ መቆየት ለዲፕሎማነት መስፈርት ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም፡፡ ወሳኝ በሆኑ ሀገራት የተሰማሩ አምባሳደሮችንና በታኮነት የተቀመጡትን ቁልፍ የኤምባሲ ሰራተኞች ማንነትና ፖለቲካዊ ስብዕና በማጤን እርምቶችን መውሰድ የግድ የሚልበት ሀገራዊ ሁኔታ ላይ እንገኛለን፡፡ እጅግ ጥልቅ እና ተለዋዋጭ ዓለማቀፋዊ፣ አህጉራዊና ቀጣናዊ የፖለቲካ ሥርዓት ባለበት ሁኔታ ብቃትን መሰረት ያደረገ የአምባሳደርነትና የዲፕሎማሲ ስምሪት ሊሰጥ ይገባል፡፡
በተረፈ በትግራይ ክልል ለደረሰው ጥፋት ዋነኛ ተጠያቂው ትህነግ ቢሆንም፤ በዚህ ሰበብ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች መቀጣት የለባቸውምና መንግስት የጀመረውን የሰብዓዊ ድጋፍና የመልሶ ማቋቋም ስራ አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ መላው የሀገራችን ህዝቦችም የኢትዮጵያ ጠላት ትህነግ እንጅ የትግራይ ህዝብ አለመሆኑን ስለተረዱ፤ ድጋፋቸውን አጠናክረው አንደሚቀጥሉ እሙን ነው፡፡
ከውጭ ሀገራት ከአውሮፓ ህብረት፣ ከአሜሪካው ስቴት ዲፓርትመንት እና ከነጩ ቤተ-መንግሥት የሚሰጡ መግለጫዎችን ከስር ከስር እየተከታተሉ ምላሽ/እርምት መስጠት ቸል ሊባል የማይገባው የመንግሥት የቤት ስራ ነው፡፡ እነዚህ ኃይሎች በተለይም የውጮቹ ምንጊዜም ቢሆን ቋሚ ጥቅም እንጅ ቋሚ ወዳጅ የላቸውም፡፡ ከላይ በመግቢያየ ላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት አሜሪካ በአመዛኙ የኢትዮጵያ ወዳጅ ሆና የቀጠለች ሀገር ነች፡፡ ከምንም በላይ ኢትዮጵያ እውነተኛውን ነጻ የገበያ ሥርዓት ለመከተል ቁርጠኝነት እያሳየች በመሆኑ አሜሪካና መሰሎቿ የኢትዮጵያ የፖለቲካል ኢኮኖሚ አጋር መሆን የሚችሉበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ እናም ሰሞነኛ መግለጫዎችን በዲፕሎማሲ ጥበብ ማለዘብና ማረቅ ይቻላል፡፡ ዋናው ነገር በቅንጭብጫቢ ጩኹት ሳይደናገጡ የዲፕሎማሲ ስራችን ላይ መበርታት መቻላችን ላይ ነው፡፡ ውጤቱ የሚወሰነው በዲፕሎማሲ ብልጫ ነው፡፡
ከሀገር ውስጥ አረናና መሰሎቹ በየጊዜው የሚያወጡት መግለጫ ከምኞት ተሻግሮ ገቢራዊ ሊሆን የሚችል አይደለም፡፡ ከትህነግ አወዳደቅ ትምህርት መውሰድ ያልፈለጉት እነዚህ ኃይሎች ትህነግ ተደምስሶም አማራ ላይ ፊጥ ሲሉ ታዝበናል፡፡ እነዚህ ወገኖች “የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ከትግራይ ክል ይውጣ“ ሲሉን የኛ ምላሽ ከየትኛዋ ትግራይ የሚል መሆን አለበት፡፡ ሕገ-ምንም አንኳ አማራው ያልተወከለበት ቢሆንም ሕገመንግሥቱ ከመጽደቁ በፊት በጉልበት ተነጥቀው የተወሰዱት ራያ፣ ወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት የፖለቲካዊ ትግራይ እንጅ ቅድመ-1983 የነበረችው የመደበኛዋ ትግራይ አካል አልነበሩም፡፡ አሁን ወደእናት ግዛታቸው ተመልሰዋል፡፡ ሕዝቡም እንደትላንቱ ሁሉ ዛሬም አማራነቱን አውጇል፡፡ እናም በሌለ ነገር ላይ ነው መግለጫ እየሰጡ ያሉት፡፡ ወልቃይትና ራያ አካባቢዎች ያለውን የአማራ ኃይል ለቆ ይውጣ ማለት ተፈጻሚነቱ የማይታሰብ፤ አጉል ምኞት ትርጉም አልባ የፖለቲካ ቅዥት ነው፡፡ አማራው በራሱ መሬት ላይ ነው ያለው፡፡ እነዚህ አካባቢዎች ዳግም ወደ ትግራይ ክልል የሚካለሉት አንድም ህዝቡ ‹እኛ ትግሬ እንጅ አማራ አይደለንም፤ ስለሆነም ወደ ትራይ መካለል እንፈልጋለን› ብሎ ከወሰነ፤ ሁለትም በጉልበት ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ተዘግቶ ያደረን ፋይል መቆስቆስ ግጭት መጫር ካልሆነ ትርፉ አይታየኝም፡፡
መዉጫ!
አሜሪካና ኢትዮጵያ በረዥሙ የግንኙነት ታሪካቸዉ ወዳጆች ተብለዉ ሊወሰዱ የሚችሉ አገሮች ናቸዉ። ስለሆነም ይሄንን የወዳጅነት ታሪክ ማስቀጠል ያስፈልጋል። በሰሞኑ ያልተገባ መግለጫ ተበሳጭተን ከመንገዳችን ልንወጣ አይገባም። በተለይም በዲፕሎማሲ ስራችን ላይ ያለዉን ክፍተት መድፈን ከቻልን፣ እንዲሁም በተለይም ዲያስፖራዉ ከሱ የሚጠበቀዉን ስራ ከሰራ፣የሰሞኑን ስንጥር አክመን ከአሜሪካ ጋር የከረመዉን ወዳጅነት አሰጠብቀን ለመቀጠል ከባድ አይመስለኝም
0 Comments:
Post a Comment
Subscribe to Post Comments [Atom]
<< Home