ተመራቂው
ተመራቂው!
የሦስት ዓመቱን ትምህርት ዘጠኝ ዓመት
የተማረው ልጅ ተመረቀ አሉ፡፡መቼም እሱ ምን
ይሳነዋል?አያሳየን ተዓምር የለም፡፡ ይኼ ልጅ
የመመረቂያ ጽሑፉን የሠራው እንዲህ በሚል
ርዕስ ነው አሉ፤ ‹‹ዩኒቨርሲቲውና የሐገሪቱ
እርምጃ(የዘጠኝ ዓመት ጉዞ ማስታወሻ!)፡፡
.
ትናንትና የተደገሰው የምርቃቱን ድግስ
በአብዛኛው ተጋብዘው የመጡት ከዘጠኝ
ዓመታት በፊት አብረውት ዩኒቨርሲቲ የገቡት
የዕድሜ እኩዮቹ ናቸው፡፡በአሁኑ ሰዓት
አብዛኛው ትዳር መሥርተው፣ልጆች ወልደው
ለማዕረግ በቅተዋል፡፡ አንድ ተጋባዥ
እንደውም ‹‹አ..ይ!!! ትንሽ ፈጠንክ እንጂ ልጄ
ዩኒቨርሲቲ ሲገባ ግቢውን ታስለምድልኝ
ነበር›› ብሎታል አሉ፡፡
.
አንድ በዕድሜ ጠና ያሉ ሽማግሌ ዓመት
እየጠበቁ ‹‹ዘንድሮ ነው ምትመረቀው?!››
እያሉ ይጠይቁት ነበር፡፡እሱም ‹‹አይ ቀጣይ
ዓመት ነው›› ይላቸዋል፡፡አሁንም ዓመት
ጠብቀው ‹‹ዘንድሮስ?›› ይሉታል፡፡ ‹‹አይ
በሚቀጥለው ዓመት ነው ጋሼ›› ይላቸዋል
ፀጉሩን እያሻሸ፡፡ ሰውዬው መጠየቁ
ሲታክታቸው ‹‹ትምህርት ሱስ ያሲዛል እንዴ?!››
ብለው ትተዉት ነበር፡፡
.
ታዲያ ትናንት ሲመረቅ በትልቅ ባልዲ የተተከለ
ጽጌረዳ አበባ በሥጣታ መልክ ይዘውለት
መጡ፡፡ ‹‹ምነው ጋሼ ይኼን እኮ ጫካ
ወስደው ቢተክሉት ሐገራዊ ግዴታዎን
ይወጡበታል፡፡እኔ ምን ላድርገው?›› አለ
በቁጣ፡፡
.
‹‹አይ እኔማ የዛሬ ስድስት ዓመት ትመረቃለህ
ብዬ ገዝቼው አይመረቅም ሲሉኝ ከምጥለው
ብዬ ቤቴ ወስጄ በባልዲ ተከልኩት፡፡አሁን
ልትመረቅ ነው ሲሉ ካላየሁ አላምንም ብዬ
ስለቸኮልኩ ከነ ባልዲው ይዤ መጣሁ፡፡
ግዴለም ተቀበለኝና ባልዲውን ስትረጋጋ
ትመልስልኛለህ፡፡››
.
በምርቃት መሰናዶው ላይ በርካታ ዓይነት
ሰዎች ታድመዋል፡፡ከዘጠኝ ዓመት በኋላ
መመረቁን ሰምተው ከውጪ
የመጡ፤መመረቁን ለማመን የተቸገሩ
መምህራን፤ለዘጠኝ ዓመታት በፆም በፀሎት
እንደሰው ለምርቃት እንዲበቃ የለፉ
የሐይማኖት አባቶች፣ለድግስ ጥርሳቸውን
ሞርደው የመጡ የሠፈር ጎረምሶች፤ይኼን
ታሪካዊ ፕሮግራም ቀርጾ ለትውልድ
ለማስተላለፍ የተቀጠሩ የቀረጻ ባለሙያዎች
እና ምንም እንኳ ትግላቸውን ቶሎ ቢጨርሱም
የትምህርት ትግሉን አብረው የጀመሩ የቀለም
ጓዶች ናወዘተ ተገኝተዋል!
.
የፕሮግራሙ መርኃ-ግብር፤ መጀመሪያ
የፈጣሪን ተዓምር በመዘከርና በማመስገን
በሐይማኖት አባቶች ተከፈተ፡፡አንድ አባት
እንዲህ አሉ ‹‹መቼም ያሬድም ሰባት ጊዜ
ከወደቀች ትል ነው ወድቆ መነሳትን
የተመለከተው፤ይኼ ልጃችን የትሏን ልፋት
ገደል በመክተት እንኳን ሰባቴ ዘጠኜም ቢሆን
ወድቆ መነሳት እንደሚቻል አሳይቶናል!››
በማስከተል እናትና አባቱ የደስታ እንባ
እየተናነቃቸው ለዘጠኝ ዓመታት ከልጃቸው ጎን
ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ሲያግዙ የነበሩ የዘመድ
አዝማድና ጎረቤት ሥም ዝርዝር ከያዘውና
ለዘጠኝ ዓመታት ከያዙት ማስታወሻ ላይ
ለሃምሳ ደቂቃ ያህል አንብበው ምስጋና
አቅርበዋል፡፡
.
ቀጥሎ ዘጠኝ ሻማዎች የተሰኩበት ኬክ
በቤተሰብና በተመራቂው ልጅ ተቆረሰ፡፡የፎቶ
መነሳት ሥነ-ሥርዓቱ የሚገርም ነበር፡፡ከልጅ
እስከ ዐዋቂ፤ከሊቅ እስከ ደቂቅ አብረውት
ፎቶውን ለታሪክ አስቀሩ፡፡
.
የመመረቂያ መጽሔቱ ላይ የጻፈው ጥቅስ
እንዲህ ይላል፤‹‹ዘጠኝ ዓመታትን ሙሉ
ተፈርዶብኝ ገብቻለሁ ብዬ እንጂ በዋስ
መውጣት አቅቶኝ እንዳልሆነ ልብ ይበሉ!››
የሚገርመኝ ነገር ማንኛውም ለምርቃት
ተጠርተን ስንሔድ እጅ እጃችንን የሚያዩት
ነገር ነው፡፡አሁን ይኼም ልጅ እንግዳ ሲመጣ
መጀመሪያ እጃቸውን ዐይቶ ደህና የሚመስል
ነገር ከያዙ እንደ ሐረግ ተጠምጥሞ ሰላም
ይላቸዋል፡፡ከዚያ ሥጦታውን ተቀብሎ ለእህቱ
ያቃብላትና ‹‹ይህቺን ለብቻ አስቀምጪያት!››
ይላታል፡፡ባዶ እጁን የሚመጣ ሲያይ ደግሞ
‹‹ሰላም እልዎት ነበር ግን እጄ ወጥ ነክቷል››
ብሎ እየሸሸ ወደ ፈረደባት እህቱ ዞሮ
‹‹ለምንድነው ይኼን ሰውዬ የጠራችሁብኝ!››
ብሎ ቱግ ይላል፡፡
.
አንድ ከውጪ ሐገር የመጣ ዘመዱ እንኳን ደስ
አለህ ካለው በኋላ ‹‹እና ስለ ሥራ ምን
አስበሃል?›› ሲል ጠየቀው፡፡
.
‹‹በርግጥ እዚህ ሐገር ሥራ ማግኘት ቀላል
ነው፤የሚከብደው ደሞዝ ያለው ሥራ ማግኘት
ነው፡፡ቢሆንም እኔ ዘጠኝ ዓመት ተምሬ ታሪክ
የሠራሁ ይመስለኛል፡፡ጂኒየስ ቡክ ላይ
ተመዝግቤ ዓለም አቀፍ ገቢ ለማግኘት ነው
ያሰብኩት›› አለ ደረቱን ወጥሮ፡፡
.
ድግሱን በቆመበት ይቃኝ ጀመር፡፡ዳንሱ የተለየ
ነው፤ሳቁ ደስታው ሌላ ዓይነት ዐውድ
ፈጥሯል፡፡ፎቶ ‹‹ብልጭ ብልጭ›› ይላል፡፡
ይኼን ተመልክቶ የኩራት ሳቅ ሊስቅ ትንሽ
ሲቀረው ከሕልሙ ነቃ፡፡ተመራቂው
የሚመረቀው በቀጣይ ዓመት ነው፡፡
0 Comments:
Post a Comment
Subscribe to Post Comments [Atom]
<< Home